1 |
አማትዋም ኑኃሚን አለቻት። ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን? |
2 |
አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል። |
3 |
እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው። |
4 |
በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል። |
5 |
ሩትም። የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለቻት። |
6 |
ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። |
7 |
ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች። |
8 |
መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች። |
9 |
እርሱም። ማን ነሽ? አለ። እርስዋም። እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ አለችው። |
10 |
ቦዔዝም አላት። ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል። |
11 |
አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ። |
12 |
የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ የቀረበ ዘመድ አለ። |
13 |
ዛሬ ሌሊት እደሪ፤ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድድ መልካም ነው፥ ዋርሳ ይሁን፤ ዋርሳ ሊሆን ባይወድድ ግን፥ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፤ እስኪነጋ ድረስ ተኚ። |
14 |
እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፤ ቦዔዝም። ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ ብሎ ነበርና ገና ሰውና ሰው ሳይተያይ ተነሣች። |
15 |
እርሱም። የለበስሽውን ኩታ አምጥተሽ ያዢው አላት፤ በያዘችም ጊዜ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፈረላት አሸከማትም። |
16 |
እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ። ወደ አማትዋም መጣች፥ አማትዋም። ልጄ ሆይ እንዴት ነሽ? አለቻት፤ እርስዋም ሰውዮው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት። |
17 |
ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ አለቻት። |
18 |
እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሰውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ዝም በዪ አለች።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |