1 |
በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም። እስከዚያም ቀን ድረስ ለዳን ነገድ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልደረሳቸውም ነበርና በዚያ ዘመን የሚቀመጡባት ርስት ይሹ ነበር። |
2 |
የዳንም ልጆች ከወገናቸው አምስት ጽኑዓን ሰዎች ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ። ሂዱ ምድሪቱንም ሰልሉ ብለው ከጾርዓና ከኤሽታኦል ሰደዱ። እነዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ። |
3 |
በሚካ ቤት አጠገብም በነበሩ ጊዜ የሌዋዊውን የጕልማሳውን ድምፅ አወቁ፤ ወደ እርሱም ቀርበው። ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህስ የምታደርገው ምንድር ነው? በዚህስ ምን አለህ? አሉት። |
4 |
እርሱም። ሚካ እንዲህ እንዲህ አደረገልኝ፥ ቀጠረኝም፥ እኔም ካህን ሆንሁለት አላቸው። |
5 |
እነርሱም። የምንሄድበት መንገድ የቀና መሆኑን እናውቅ ዘንድ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት። |
6 |
እርሱም። የምትሄዱበት መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና በደኅና ሂዱ አላቸው። |
7 |
አምስቱም ሰዎች ሄዱ ወደ ሌሳም መጡ፥ በውስጡም የነበሩትን ሕዝብ ተዘልለው አዩአቸው፥ አንደ ሲዶናውያንም ልማድ ጸጥ ብለው ተዘልለው ተቀምጠው ነበር፤ የሚያስቸግራቸውም የሚገዛቸውም አልነበረም፥ ከሲዶናውያንም ርቀው ከሰውም ሁሉ ተለይተው ለብቻቸው ይኖሩ ነበር። |
8 |
ወደ ወንድሞቻቸውም ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል ተመለሱ፤ ወንድሞቻቸውም። ምን ወሬ ይዛችኋል? አሉአቸው። |
9 |
እነርሱም ምድሪቱን እግጅ መልካም እንደ ሆነች አይተናልና ተነሡ፥ በእነርሱ ላይ እንውጣ፤ እናንተ ዝም ትላላችሁን? ትሄዱ ዘንድ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ። |
10 |
በሄዳችሁ ጊዜ ተዘልለው ወደ ተቀመጡ ሕዝብ ትደርሳላችሁ፥ ምድሪቱም ሰፊ ናት፤ እግዚአብሔርም በምድር ካለው ነገር ሁሉ አንዳች የማይጎድልበትን ስፍራ በእጃችሁ ሰጥቶአል አሉ። |
11 |
ከዳን ወገንም የጦር ዕቃ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከዚያ ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሥተው ሄዱ። |
12 |
ወጥተውም በይሁዳ ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር ተብሎ ተጠራ፤ እነሆም፥ ከቂርያትይዓሪም በስተ ኋላ ነው። |
13 |
ከዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር አለፉ፤ ወደ ሚካም ቤት መጡ። |
14 |
የሌሳን ምድር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም ወንድሞቻቸውን። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድና ተራፊም፥ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስልም እንዳሉ ታውቃላችሁን? አሁንም የምታደርጉትን ምከሩ ብለው ተናገሩአቸው። |
15 |
ከመንገዱም ፈቀቅ ብለው ጕልማሳው ሌዋዊ ወደ ነበረበት ወደ ሚካ ቤት መጡ፥ ደኅንነቱንም ጠየቁት። |
16 |
የጦር ዕቃ የታጠቁት፥ ከዳን ልጆችም የሆኑት ስድስቱ መቶ ሰዎች በደጃፉ አጠገብ ቆመው ነበር። |
17 |
ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወጥተው ወደዚያ ገቡ፤ የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም የጦር ዕቃ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በደጃፉ አጠገብ ቆሞ ነበር። |
18 |
እነዚህም ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም በወሰዱ ጊዜ፥ ካህኑ። ምን ታደርጋላችሁ? አላቸው። |
19 |
እነርሱም። ዝም በል፥ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፥ ከእኛም ጋር መጥተህ አባትና ካህን ሁንልን፤ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል? አሉት። |
20 |
ካህኑም በልቡ ደስ አለው፥ ኤፉዱንም ተራፊሙንም የተቀረጸውንም ምስል ወሰደ፥ በሕዝቡም መካከል ሄደ። |
21 |
እነርሱም ዞረው ሄዱ፥ ሕፃናቶችንና ከብቶችን ዕቃዎችንም በፊታቸው አደረጉ። |
22 |
ከሚካም ቤት በራቁ ጊዜ የሚካ ጐረቤቶች ተሰበሰቡ፥ የዳንም ልጆች ተከትለው ደረሱባቸው። |
23 |
ወደ ዳንም ልጆች ጮኹ፥ የዳንም ልጆች ፊታቸውን መልሰው ሚካን። የምትጮኸው ምን ሆነህ ነው? አሉት። |
24 |
እርሱም። የሠራኋቸውን አማልክቴን ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችኋል፤ ሌላ ምን አለኝ? እናንተስ። ምን ሆነሃል እንዴት ትሉኛላችሁ? አለ። |
25 |
የዳንም ልጆች። የተቈጡ ሰዎች እንዳይወድቁብህ ነፍስህም የቤተ ሰቦችህም ነፍስ እንዳይጠፋብህ፥ ድምፅህን በእኛ መካከል አታሰማ አሉት። |
26 |
የዳንም ልጆች መንገዳቸውን ሄዱ፤ ሚካም ከእርሱ እንደ በረቱ ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። |
27 |
እነርሱም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ለእርሱ የነበረውን ካህን ይዘው ወደ ሌሳ፥ ጸጥ ብሎ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ፥ መጡ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት። |
28 |
ከተማይቱ ከሲዶና ራቅ ያለች ነበረችና፥ እነርሱም ከሌሎች ሰዎች ተለይተው ብቻቸውን ይኖሩ ነበርና የሚታደግ አልነበራቸውም። ሌሳም በቤትሮዖብ አጠገብ ባለች ሸለቆ ውስጥ ነበረች። ከተማይቱንም ሠርተው ተቀመጡባት። |
29 |
ከተማይቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ የከተማይቱም ስም አስቀድሞ ሌሳ ነበረ። |
30 |
የዳንም ልጆች የተቀረጸውን ምስል ለራሳቸው አቆሙ፤ የሙሴም ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፥ እርሱና ልጆቹ የአገሩ ሰዎች እስከሚማረኩበት ቀን ድረስ የዳን ነገድ ካህናት ነበሩ። |
31 |
ሚካም ያደረገውን የተቀረጸ ምስል የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ ባለበት ዘመን ሁሉ አቆሙ። a
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |