1 |
ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። |
2 |
ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። |
3 |
አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። |
4 |
ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብፅ ወረዱ። |
5 |
ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብፅን ቀሠፍሁ፤ ከዚያም በኋላ አወጣኋቸው። |
6 |
አባቶቻችሁንም ከግብፅ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። |
7 |
ወደ እግዚአብሔርም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፤ ዓይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። |
8 |
እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። |
9 |
የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። |
10 |
እኔ ግን በለዓምን መስማት አልወደድሁም፤ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። |
11 |
ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። |
12 |
በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፥ በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። |
13 |
ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ። |
14 |
አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ። |
15 |
እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን። |
16 |
ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ። እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፤ |
17 |
እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። |
18 |
እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱም የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እግዚአብሔርን እናመልካለን። |
19 |
ኢያሱም ሕዝቡን። እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። |
20 |
እግዚአብሔርን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችሁማል አላቸው። |
21 |
ሕዝቡም ኢያሱን። እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን አሉት። |
22 |
ኢያሱም ሕዝቡን። እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ አላቸው፤ እነርሱም። ምስክሮች ነን አሉ። |
23 |
እርሱም። አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አዘንብሉ አላቸው። |
24 |
ሕዝቡም ኢያሱን። አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ድምፁንም እንሰማለን አሉት። |
25 |
በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። |
26 |
ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። |
27 |
ኢያሱም ለሕዝቡ። እነሆ፥ የተናገረንን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፤ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል አላቸው። |
28 |
ኢያሱም ሕዝቡን በእያንዳንዱ ወደ ርስቱ ሰደደ። |
29 |
እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። |
30 |
በተራራማውም በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። |
31 |
ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ። |
32 |
የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ያወጡትን የዮሴፍን አጥንት ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በግ በገዛው እርሻ በሴኬም ቀበሩት፤ እርሻውም ለዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ። |
33 |
የአሮንም ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ለልጁ ለፊንሐስ በተሰጠችው በጊብዓ መሬት ቀበሩት።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |