1 |
እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን። |
2 |
እንደዚህም ሲሆን፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል። |
3 |
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ |
4 |
በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። |
5 |
ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። |
6 |
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ። ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። |
7 |
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? |
8 |
አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር። |
9 |
ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና። |
10 |
እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን። |
11 |
እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ |
12 |
በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ |
13 |
እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል። |
14 |
እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። |
15 |
በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። |
16 |
እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። |
17 |
ስለዚህ የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፥ እኔም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደማስተምር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚሆነውን መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል። |
18 |
አንዳንዱ ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤ |
19 |
ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፥ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤ |
20 |
የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። |
21 |
ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |