1 |
እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። |
2 |
ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። |
3 |
እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ |
4 |
በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። |
5 |
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። |
6 |
በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል። |
7 |
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። |
8 |
ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። |
9 |
አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። |
10 |
እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። |
11 |
ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ። |
12 |
እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። |
13 |
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። |
14 |
እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። |
15 |
ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። |
16 |
እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ። |
17 |
እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ። |
18 |
ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። |
19 |
ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። |
20 |
ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። |
21 |
ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ሰለ ስሜ ያደርጉባችኋል። |
22 |
እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም። |
23 |
እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። |
24 |
ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደረግሁ፥ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል። |
25 |
ነገር ግን በሕጋቸው። በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። |
26 |
ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ |
27 |
እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |