1 |
ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ። |
2 |
በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር። |
3 |
አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። |
4 |
ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። |
5 |
ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። |
6 |
ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም። ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? |
7 |
ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ። |
8 |
ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው። በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ? |
9 |
ሽባውን። ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? |
10 |
ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ |
11 |
ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። |
12 |
ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፥ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና። እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ። |
13 |
ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። |
14 |
ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው። |
15 |
በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ ይከተሉትም ነበር። |
16 |
ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ። ከቀራ ጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ። |
17 |
ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው። |
18 |
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም። የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። |
19 |
ኢየሱስም አላቸው። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም። |
20 |
ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ። |
21 |
በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። |
22 |
በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ። |
23 |
በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። |
24 |
ፈሪሳውያንም። እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት። |
25 |
እርሱም። ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ |
26 |
ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። |
27 |
ደግሞ። ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ |
28 |
እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |