1 |
ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። |
2 |
ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱ በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አይስበር፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ። |
3 |
ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ |
4 |
አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። |
5 |
አባትዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባትዋ ከልክሎአታልና እግዚአብሔር ይቅር ይላታል። |
6 |
በተሳለችም ጊዜ ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበት ነገር ከአፍዋ በወጣ ጊዜ ባል ያገባች ብትሆን፥ |
7 |
ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናል። |
8 |
ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ በእርስዋ ላይ ያለውን ስእለትዋን ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበትን የአፍዋን ነገር ከንቱ ያደርገዋል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል። |
9 |
ባልዋ የሞተባት ወይም የተፋታች ግን ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸኑባታል። |
10 |
ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ |
11 |
ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት ባይከለክላትም፥ ስእለትዋ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። |
12 |
ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ከንቱ ቢያደርገው፥ ስለ ስእለትዋ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ ከአፍዋ የወጣው ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከንቱ አድርጎታል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል። |
13 |
ስእለትዋን ሁሉ ነፍስዋንም የሚያዋርደውን መሐላ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፥ ባልዋም ከንቱ ያደርገዋል። |
14 |
ባልዋ ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለትዋን ሁሉ በእርስዋም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ አጽንቶታል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል። |
15 |
ከሰማው በኋላ ግን ከንቱ ቢያደርገው ኃጢአትዋን ይሸከማል። |
16 |
እርስዋ በብላቴንነትዋ ጊዜ በአባትዋ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው ሥርዓት ይህ ነው።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |