1 |
በለዓምም ባላቅን። ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ አለው። |
2 |
ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ። |
3 |
በለዓምም ባላቅን። በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ አለው። ወደ ጉብታም ሄደ። |
4 |
እግዚአብሔርም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ እርሱም። ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ አለው። |
5 |
እግዚአብሔርም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው። |
6 |
ወደ እርሱም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ አለቆች ሁሉ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር። |
7 |
ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ ብሎ። |
8 |
እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? |
9 |
በአምቦች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም። |
10 |
የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልስ እርቦ ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን። |
11 |
ባላቅም በለዓምን። ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው። |
12 |
እርሱም መልሶ። በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው። |
13 |
ባላቅም። በዚያ ሆነህ ታያቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ አለው። |
14 |
ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ። |
15 |
ባላቅንም። እኔ ወደዚያ ለመገናኘት ስሄድ በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ አለው። |
16 |
እግዚአብሔርም በለዓምን ተገናኘ፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው። |
17 |
ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም። እግዚአብሔር የተናገረው ምንድር ነው? አለው። |
18 |
ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ ስማ፤ የሴፎር ልጅ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ |
19 |
ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን? |
20 |
እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም። |
21 |
በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ። |
22 |
እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው። |
23 |
በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል። እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል። |
24 |
እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን አስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም። |
25 |
ባላቅም በለዓምን። ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው አለው። |
26 |
በለዓምም መልሶ ባላቅን። እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን? አለው። |
27 |
ባላቅም በለዓምን። ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድዳል አለው። |
28 |
ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ላይ በለዓምን ወሰደው። |
29 |
በለዓምም ባላቅን። በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ አለው። |
30 |
ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |