1 |
ተመልሼም ዓይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አራት ሰረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ። |
2 |
በፊተኛው ሰረገላ መጋላ ፈረሶች፥ በሁለተኛውም ሰረገላ ዱሪ ፈረሶች ነበሩ፥ |
3 |
በሦስተኛውም ሰረገላ አምባላይ ፈረሶች፥ በአራተኛውም ሰረገላ ቅጥልጣል ፈረሶች ነበሩ። |
4 |
ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። |
5 |
መልአኩም መልሶ። እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ናቸው። |
6 |
ዱሪ ፈረሶች ያሉበት ወደ ሰሜን ይወጣል፤ አምባላዮቹም ከእነርሱ በኋላ ይወጣሉ፥ ቅጥልጣሎችም ወደ ደቡብ ይወጣሉ አለኝ። |
7 |
መጋላዎቹም ደግሞ ወጡ በምድርም ይመላለሱ ዘንድ ለመሄድ ይፈልጉ ነበር፤ እርሱም። ሂዱ፥ በምድር ላይ ተመላለሱ አለ። እነርሱም በምድር ላይ ተመላለሱ። |
8 |
ጮኾም። እነሆ፥ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት እነርሱ መንፈሴን በሰሜን ምድር ላይ አሳርፈዋል ብሎ ተናገረኝ። |
9 |
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
10 |
ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ ከዮዳኤም ውሰድ፤ በዚያም ቀን መጥተህ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ግባ። |
11 |
ብርንና ወርቅን ከእነርሱ ውሰድ፥ አክሊሎችንም ሥራ፤ በታላቁም ካህን በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋቸው፥ |
12 |
እንዲህም በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ቍጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል። |
13 |
እርሱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይሸከማል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፥ የሰላምም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል። |
14 |
አክሊሎችም ለሔሌምና ለጦብያ ለዮዳኤም ለሶፎንያስም ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ ለመታሰቢያ ይሆናሉ። |
15 |
በሩቅም ያሉት መጥተው የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቃችሁ ብትሰሙ ይህ ይሆናል።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |