1 |
በኋለኛው ዝናብ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዝናቡን ለምኑ፤ እግዚአብሔር መብረቅ ያደርጋል፤ እርሱም የበልግ ዝናብን ለእያንዳንዱም በሜዳ ውስጥ ሣርን ይሰጣል። |
2 |
ተራፊም ከንቱነትን ተናግረዋልና፥ ምዋርተኞችም ውሸትን አይተዋልና፤ ሕልምንም የሚያዩ በሐሰት ተናግረዋል፥ በከንቱም ያጽናናሉ፤ እረኛም የላቸውምና እንደ በጎች ተቅበዝብዘዋል ተጨንቀውማል። |
3 |
ቍጣዬ በእረኞች ላይ ነድዶአል፥ አውራ ፍየሎችንም እቀጣለሁ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም የይሁዳን ቤት መንጋውን ጐብኝቶአል፥ በሰልፍም ውስጥ እንዳለ እንደ ክብሩ ፈረስ ያደርጋቸዋል። |
4 |
ከእርሱ ዘንድ የማዕዘኑ ድንጋይ፥ ከእርሱም ዘንድ ችንካሩ፥ ከእርሱም ዘንድ የሰልፉ ቀስት፥ ከእርሱም ዘንድ አስገባሪው ሁሉ በአንድ ላይ ይመጣሉ። |
5 |
በሰልፍም ጊዜ ጠላቶቻቸውን በመንገድ ጭቃ ውስጥ እንደሚረግጡ ኃያላን ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነውና ይዋጋሉ፥ ፈረሰኞችም ያፍራሉ። |
6 |
ወድጃቸዋለሁና የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፥ የዮሴፍንም ቤት አድናለሁ፤ አደላድላቸዋለሁም፤ እመልሳቸዋለሁ፤ እኔም አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፥ እኔም እሰማቸዋለሁና እንዳልጣልኋቸው ይሆናሉ። |
7 |
የኤፍሬምም ሰዎች እንደ ኃያላን ይሆናሉ፥ ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ደስ ይለዋል፤ ልጆቻቸውም አይተው ደስ ይላቸዋል፥ ልባቸውም በእግዚአብሔር ሐሤት ያደርጋል። |
8 |
ተቤዥቼአቸዋለሁና በፉጨት ጠርቼ እሰበስባቸዋለሁ፤ ቀድሞም በዝተው እንደ ነበሩ ይበዛሉ። |
9 |
በአሕዛብም መካከል ብዘራቸው እንኳ በሩቅ አገር ሳሉ ያስቡኛል፥ ከልጆቻቸውም ጋር በሕይወት ይኖራሉ፥ ይመለሱማል። |
10 |
ከግብጽም ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ ምድር አመጣቸዋለሁ፥ የሚበቃም ቦታ አይገኝላቸውም። |
11 |
እርሱም በጭንቅ ባሕር ያልፋል፥ የባሕርንም ሞገድ ይመታል፥ የወንዙም ጥልቅ ሁሉ ይደርቃል፤ የአሦርም ትዕቢት ይዋረዳል፥ የግብጽም በትረ መንግሥት ይርቃል። |
12 |
በአምላካቸው በእግዚአብሔር አበረታቸዋለሁ፥ በስሙም ይመካሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |