1 |
የሚቀጠቅጥ በአንተ ላይ ወጥቶአል፤ ምሽግን ጠብቅ፥ መንገድንም ሰልል፤ ወገብህን አጽና፥ ኃይልህንም እጅግ አበርታ። |
2 |
ዘራፊዎች ዘርፈዋቸዋልና፥ የወይናቸውንም አረግ አጥፍተዋልና እግዚአብሔር የያዕቆብን ክብር እንደ እስራኤል ክብር ይመልሳል። |
3 |
የኃያላኑ ጋሻ ቀልቶአል፥ ጽኑዓንም ቀይ ልብስ ለብሰዋል። እርሱም በሚያዘጋጅበት ቀን ሰረገሎች እንደ እሳት ይንቦገቦጋሉ፤ የጦሩም ሶመያ ይወዛወዛል። |
4 |
ሰረገሎች በመንገድ ላይ ይነጕዳሉ፥ አደባባይም ይጋጫሉ፤ መልካቸው እንደ ፋና ነው፥ እንደ መብረቅም ይከንፋሉ። |
5 |
መሳፍንቱን ያስባል፤ በአረማመዳቸው ይሰናከላሉ፤ ፈጥነው በቅጥርዋ ላይ ይወጣሉ፥ መጠጊያም ተዘጋጀለት። |
6 |
የወንዞቹም መዝጊያዎች ተከፈቱ፥ የንጉሡ ቤትም ቀለጠች። |
7 |
ንግሥት ተገለጠች፥ ተማረከችም፥ ሴቶች ባሪያዎችዋም እንደ ርግብ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ ዋይ ዋይ ይላሉ። |
8 |
ነነዌ ግን ከዱሮ ዘመን ጀምራ እንደ ተከማቸ ውኃ ነበረች፤ አሁን ግን ይሸሻሉ፤ እነርሱም። ቁሙ፥ ቁሙ ይላሉ፥ ነገር ግን የሚመለስ የለም። |
9 |
መዝገብዋ መጨረሻ የለውምና፥ የከበረውም የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቈጠርምና ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ። |
10 |
ባዶና ባድማ ምድረ በዳም ሆናለች፤ ልብ ቀልጦአል፥ ጕልበቶችም ተብረክርከዋል፤ በወገብም ሁሉ ሕማም አለ፥ የሰዎችም ሁሉ ፊት ጠቍሮአል። |
11 |
የአንበሾችም መደብ፥ የአንበሾችም ደቦል የሚሰማራበት፥ አንበሳውና አንበሳይቱ ግልገሉም ሳይፈሩ የሚሄዱት ስፍራ ወዴት ነው? |
12 |
አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም ሰበረላቸው ዋሻውን በንጥቂያ፥ መደቡንም በቅሚያ ሞልቶታል። |
13 |
እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰረገሎችዋንም አቃጥዬ አጤሳለሁ፥ ሰይፍም የአንበሳ ደቦሎችሽን ይበላቸዋል፤ ንጥቂያሽንም ከምድር አጠፋለሁ፥ የመልክተኞችሽን ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ አይሰማም።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |