1 |
እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
2 |
የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው። የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፤ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። |
3 |
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ አሕዛብ ጉባኤ መረቤን እዘረጋብሃለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል። |
4 |
በምድርም ላይ እተውሃለሁ፥ በምድረ በዳም ፊት እጥልሃለሁ፥ የሰማይንም ወፎች ሁሉ አሳርፍብሃለሁ፥ የምድርንም አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ። |
5 |
ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ። |
6 |
የምትዋኝባትንም ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖችም ከአንተ ይሞላሉ። |
7 |
ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም። |
8 |
የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
9 |
በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ጥፋትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ። |
10 |
ብዙም አሕዛብን አስደንቅብሃለሁ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ስለ አንተ እጅግ አድርገው ይፈራሉ፤ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣል። |
11 |
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል። |
12 |
በኃያላን ሰይፍ የሕዝብህን ብዛት እጥላለሁ፤ ሁሉ የአሕዛብ ጨካኞች ናቸው፤ የግበጽንም ትዕቢት ያጠፋሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል። |
13 |
በብዙም ውኃ አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም የእንስሳም ኮቴ አይረግጠውም። |
14 |
በዚያን ጊዜ ውኃቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
15 |
የግብጽንም ምድር ባድማና ውድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በቀሠፍሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |
16 |
የሚያለቅሱበት ልቅሶ ይህ ነው፤ የአሕዛብ ቈነጃጅት ያለቅሱበታል፤ ስለ ግብጽና ስለ ብዛትዋ ሁሉ ያለቅሱበታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
17 |
እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
18 |
የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርስዋንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው። |
19 |
በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ። |
20 |
በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እርስዋንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ። |
21 |
የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፤ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል። |
22 |
አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፤ መቃብራቸው በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም በሰይፍ ወድቀው ተገደሉ። |
23 |
መቃብራቸው በጕድጓዱ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል። |
24 |
ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። |
25 |
በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፤ መቃብርዋ በዙሪያዋ ነው ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ በሕያዋንም ምድር ያስፈሩ ነበር ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል። |
26 |
ሞሳሕና ቶቤል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም ሳይገረዙ በሰይፍ ተገድለዋል፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ነበርና። |
27 |
በሕያዋንም ምድር ኃያላኑን ያስፈሩ ነበርና መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሲኦል ከወረዱ፥ ሰይፋቸውንም ከራሳቸው በታች ካደረጉ፥ ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ከሆነ ጋር ከወደቁ ካልተገረዙ ኃያላን ጋር ይተኛሉ። |
28 |
አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ። |
29 |
ኤዶምያስና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር በኃይላቸው ተኝተዋል፤ ካልተገረዙትና ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ይተኛሉ። |
30 |
የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፤ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። |
31 |
በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |
32 |
መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |