1 |
አንተም በእስራኤል አለቆች ላይ ይህን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በል። |
2 |
እናትህ ምን ነበረች? አንበሳ ነበረች፤ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፤ በደቦል አንበሶች መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች። |
3 |
ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ንጥቂያንም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ። |
4 |
አሕዛብም ወሬውን ሰሙ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፥ በሰንሰለትም አድርገው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት። |
5 |
እርስዋም እንደ ደከመችና ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው። |
6 |
እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ ደቦል አንበሳም ሆነ፤ ንጥቂያም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ። |
7 |
ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረሰ፤ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድሪቱና ሞላዋ ጠፋች። |
8 |
አሕዛብም በዙሪያው ከየአገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፤ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ በጕድጓዳቸውም ተያዘ። |
9 |
በሰንሰለትም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ አምባ አገቡት። |
10 |
እናትህ በመልክህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድ ነበረች፤ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች። |
11 |
ለእርስዋም ብርቱዎች በትሮች ነበሩአት እነርሱም ለነገሥታት በትሮች ነበሩ። ቁመታቸውም በዛፎች ቅርንጫፎች መካከል ረዘመ፥ በጫፎቻቸውም ብዛትና በርዝመታቸው ታዩ። |
12 |
ነገር ግን በመዓት ተነቀለች ወደ መሬትም ተጣለች የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፥ እሳትም በላቻቸው። |
13 |
አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች። |
14 |
ከጫፎችዋም በትሮች እሳት ወጣች ፍሬዋንም በላች፥ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |