1 |
ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። |
2 |
በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፥ ይህንም ቃል እንዲህ ብለህ ተናገር። እግዚአብሔርን ልታመልኩ በእነዚህ በሮች የምትገቡ ከይሁዳ ያላችሁ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። |
3 |
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ በዚህም ስፍራ አሳድራችኋለሁ። |
4 |
የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ ይህ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ። |
5 |
መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፥ |
6 |
መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትገፉ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም ሊሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፥ |
7 |
ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር በዚህ ስፍራ አሳድራችኋለሁ። |
8 |
እነሆ፥ በማትረቡበት በሐሰት ቃል ታምናችኋል። |
9 |
ትሰርቃላችሁ፥ ትገድላላችሁ፥ ታመነዝራላችሁ፥ በሐሰትም ትምላላችሁ፥ ለበኣልም ታጥናላችሁ፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁ፤ |
10 |
መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ። ይህን አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ አላደረግንም አላችሁ። |
11 |
ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
12 |
ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደ ነበረው ስፍራዬ ሂዱ፥ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትን እዩ። |
13 |
አሁንም ይህን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ በማለዳም ተነሥቼ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥ |
14 |
ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ አደርጋለሁ። |
15 |
የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፥ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ። |
16 |
እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው። |
17 |
እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን? |
18 |
ያስቈጡኝ ዘንድ፥ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን እንዲያፈስሱ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፥ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፥ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ። |
19 |
እኔን ያስቈጣሉን? ይላል እግዚአብሔር፤ ለፊታቸውስ እፍረት አይደለምን? |
20 |
እንግዲህም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፤ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። |
21 |
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለሌላ መሥዋዕታችሁ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፥ ሥጋውንም ብሉ። |
22 |
ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም። |
23 |
ነገር ግን። ቃሌን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። |
24 |
ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። |
25 |
አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። |
26 |
ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ። |
27 |
በዚህም ቃል ሁሉ ትነግራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም። |
28 |
አንተም። የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፤ እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ተቈርጦአል ትላቸዋለህ። |
29 |
እግዚአብሔር የቍጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጕርሽን ቍረጪ፥ ጣዪውም፥ በወናዎች ኮረብቶችም ላይ አሙሺ። |
30 |
የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ርኵሰታቸውን አኑረዋል። |
31 |
እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያለችውን የቶፌትን መስገጃዎች ሠረተዋል። |
32 |
ስለዚህ፥ እነሆ፥ ስፍራ ከማጣት የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። |
33 |
የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራራቸውም የለም። |
34 |
ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ አጠፋለሁ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |