1 |
እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራችን መታጠቂያ ለአንተ ግዛ፥ ወገብህንም ታጠቅባት፤ በውኃውም ውስጥ አትንከራት። |
2 |
እንደ እግዚአብሔርም ቃል መታጠቂያን ገዛሁ ወገቤንም ታጠቅሁባት። |
3 |
ሁለተኛም ጊዜ። የገዛሃትን በወገብህ ያለችውን መታጠቂያ ወስደህ ተነሥ፥ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፥ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣልኝ። |
4 |
*** |
5 |
እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ ሄድሁ በኤፍራጥስም አጠገብ ሸሸግኋት። |
6 |
ከብዙ ቀንም በኋላ እግዚአብሔር። ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም ትሸሽጋት ዘንድ ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ አለኝ። |
7 |
እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፥ ከሸሸግሁበትም ስፍራ መታጠቂያይቱን ወሰድሁ። እነሆም፥ መታጠቂያይቱ ተበላሽታ ነበር፥ ለምንም አልረባችም። |
8 |
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ |
9 |
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አበላሻለሁ። |
10 |
ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ የሚሉ፥ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ያመልኩአቸውና ይሰግዱላቸው ዘንድ ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንዳማትረባ እንደዚች መታጠቂያ ይሆናሉ። |
11 |
መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደምትጣበቅ፥ እንዲሁ ሕዝብና ስም ምስጋናና ክብር ይሆኑልኝ ዘንድ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን አልሰሙም። |
12 |
ስለዚህ።የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል ብለህ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም። ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንዲሞላ በውኑ እኛ አናውቅምን? ይሉሃል። |
13 |
አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት ካህናቱንም ነቢያቱንም በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። |
14 |
ሰውንም በሰው ላይ፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፥ እቀጠቅጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፥ አላዝንም፥ አልምርም። |
15 |
ስሙ፥ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና አትታበዩ። |
16 |
ሳትጨልም እግራችሁም በጨለመችው ተራራ ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨለማ ሳይለውጠው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። |
17 |
ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የእግዚአብሔርም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ ታነባለች፥ እንባንም ታፈስሳለች። |
18 |
ለንጉሡና ለንጉሥ እናት ለእቴጌይቱ። የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ተዋርዳችሁ ተቀመጡ በል። |
19 |
የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፥ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፥ ፈጽሞ ተማርኮአል። |
20 |
ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፤ ለአንቺ የተሰጠ መንጋ፥ የተዋበ መንጋሽ፥ ወዴት አለ? |
21 |
ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? |
22 |
በልብሽም። እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረሰብኝ? ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል። |
23 |
በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ። |
24 |
ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ። |
25 |
ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽ የለካሁልሽም እድል ፈንታ ይህ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር። |
26 |
ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። |
27 |
አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የግልሙትናሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |