1 |
እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። |
2 |
የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። |
3 |
እነርሱም። ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል። ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ኃይል የለም። |
4 |
ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ አሉት። |
5 |
እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ። |
6 |
ኢሳይያስም። ለጌታችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። |
7 |
እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬንም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት አላቸው። |
8 |
የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በልብና ሲዋጋ አገኘው። |
9 |
እርሱም። የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቶአል የሚል ወሬ ሰማ። በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ |
10 |
እንዲህ ሲል። ለይሁዳ ንጉሠ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። |
11 |
እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? |
12 |
አባቶቼ ያጠፉአቸውን ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፊስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? |
13 |
የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ? |
14 |
ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። |
15 |
ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ። |
16 |
አቤቱ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። |
17 |
አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬም ቃል ስማ። |
18 |
አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ አገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፥ |
19 |
አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። |
20 |
እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን። |
21 |
የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ለምነሃልና |
22 |
እግዚአብሔር ስለ እርሱ የተናገረው ቃል ይህ ነው። ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ራስዋን ነቅንቃብሃለች። |
23 |
የተገዳደርኸው የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግህበት ዓይንህንስ ወደ ላይ ያነሣህበት ማን ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው። |
24 |
አንተም። በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ ላይ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ ከፍታውም ዳርቻ ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ። |
25 |
ቈፈርሁም ውኃም ጠጣሁ የግብጽንም ወንዞች ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ ብለህ በባሪያዎችህ እጅ በጌታ ላይ ተገዳደርህ። |
26 |
እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ። |
27 |
ስለዚህ የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሎአል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለመለመም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታው እህል ሆነዋል። |
28 |
እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቍጣ አውቄአለሁ። |
29 |
ቍጣህና ትዕቢትህ ወደጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፥ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ። |
30 |
ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ ታጭዱማላችሁ፥ ወይንም ትተክላላችሁ ፍሬውንም ትበላላችሁ። |
31 |
ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል። |
32 |
ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ከጽዮንም ተራራ ያመለጡት ይወጣሉና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። |
33 |
ስለዚህም እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። |
34 |
በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፥ ወደዚችም ከተማ አይመጣም ይላል እግዚአብሔር። |
35 |
ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ። |
36 |
የእግዚአብሔርም መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። |
37 |
የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። |
38 |
በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |