1 |
እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፤ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃል። |
2 |
አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፥ የእስራኤልም ቤት በእግዚአብሔር ምድር እንደ ሎሌዎችና እንደ ገረዶች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ የማረኩአቸውን ይማርካሉ፥ አስጨናቂዎችንም ይገዛሉ። |
3 |
በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከኀዘንህና ከመከራህ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። |
4 |
ይህንም ምሳሌ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ እንዲህም ትላለህ። አስጨናቂ እንዴት ዐረፈ! አስገባሪም እንዴት ጸጥ አለ! |
5 |
አሕዛብንም በመዓትና በማያቋርጥ መምታት የመታውን፥ አሕዛብንም ባልተከለከለ መከራ በቍጣው የገዛውን የኀጥኣንን በትር የአለቆችንም ዘንግ እግዚአብሔር ሰብሮአል። |
6 |
*** |
7 |
ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች። |
8 |
ጥድና የሊባኖስ ዝግባ። አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው። |
9 |
ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የሞቱትንም፥ የምድርን ታላላቆች ሁሉ፥ ለአንተ አንቀሳቀሰች፥ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው አስነሣች። |
10 |
እነዚህ ሁሉ። አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃልን? እኛንስ መስለሃልን? ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤ |
11 |
በበታችህም ብል ተነጥፎአል፥ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል ብለው ይመልሱልሃል። |
12 |
አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ! |
13 |
አንተን በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ |
14 |
ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። |
15 |
ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ። |
16 |
የሚያዩህ ይመለከቱሃልና። በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ |
17 |
ዓለሙን ሁሉ ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ ምርከኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልሰደደ ሰው ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል። |
18 |
የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። |
19 |
አንተ ግን እንደ ተጠላ ቅርንጫፍ ከመቃብርህ ተጥለሃል፤ በሰይፍም የተወጉት፥ ተገድለውም ወደ ጕድጓዱ ድንጋዮች የወረዱት ከድነውሃል፤ እንደ ተረገጠም ሬሳ ሆነሃል። |
20 |
ምድርህን አጥፍተሃልና፥ ሕዝብህንም ገድለሃልና ከእነርሱ ጋር በመቃብር በአንድነት አትሆንም፤ የክፉዎች ዘር ለዘላለም የተጠራ አይሆንም። |
21 |
እንዳይነሡም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በከተሞች እንዳይሞሉ ስለ አባቶቻቸው በደል ለልጆቹ ሞትን አዘጋጁላቸው። |
22 |
በእነርሱ ላይ እነሣለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም እቈርጣለሁ ይላል እግዚአብሔር። |
23 |
የጃርት መኖርያ የውኃም መቋሚያ አደርጋታለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |
24 |
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል። እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፥ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል። |
25 |
አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፥ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፥ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል። |
26 |
በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት። |
27 |
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው? |
28 |
ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት ይህ ሸክም ሆነ። |
29 |
ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። |
30 |
የድሆችም የበኵር ልጆች ይሰማራሉ፥ ችግረኞችም ተዘልለው ይተኛሉ፤ ሥርህንም በራብ እገድላለሁ፥ ቅሬታህም ይገደላል። |
31 |
አንተ በር ሆይ፥ ወዮ በል አንቺም ከተማ ሆይ፥ ጩኺ፤ ፍልስጥኤም ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይመጣል ከጭፍራውም ተለይቶ የሚቀር የለም። |
32 |
ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መመለስ ይገባል? እግዚአብሔር ጽዮንን እንደ መሠረተ፥ የሕዝቡም ችግረኞች በእርስዋ ውስጥ እንደሚጠጉ ነው።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |