1 |
ጻድቃንና ጠቢባን ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፤ ፍቅር ወይም ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም ሁሉ ወደ ፊታቸው ነው። |
2 |
የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፤ እንደ መልካሙ ሰው እንዲሁ ኃጢአተኛው፥ እንደ መሐለኛው ሰው እንዲሁ መሐላን የሚፈራው ነው። |
3 |
አንድ ድርሻ ሁሉን እንዲያገኝ ከፀሐይ በታች በተደረገው ሁሉ ይህ ነገር ክፉ ነው፤ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ነው፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። |
4 |
ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። |
5 |
ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። |
6 |
ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። |
7 |
እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። |
8 |
ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። |
9 |
በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። |
10 |
አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። |
11 |
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። |
12 |
ሰውም ጊዜውን አያውቅም፤ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ። |
13 |
ከፀሐይ በታችም ይህን ጥበብ አየሁ፥ እርስዋም በእኔ ዘንድ ታላቅ መሰለችኝ። |
14 |
ታናሽ ከተማ ነበረች፥ ጥቂቶች ሰዎችም ነበሩባት፤ ታላቅ ንጉሥም መጣባት ከበባትም፥ ታላቅ ግንብም ሠራባት። |
15 |
ጠቢብ ድሀ ሰውም ተገኘባት፥ ያችንም ከተማ በጥበቡ አዳናት፤ ያን ድሀ ሰው ግን ማንም አላሰበውም። |
16 |
እኔም። ከኃይል ይልቅ ጥበብ ትበልጣለች፤ የድሀው ጥበብ ግን ተናቀች ቃሉም አልተሰማችም አልሁ። |
17 |
በሰነፎች መካከል ከሚጮኽ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች። |
18 |
ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፤ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |