1 |
እናቱ እርሱን ያስተማረችበት የማሣ ንጉሥ የልሙኤል ቃል። |
2 |
ልጄ ሆይ፥ ምንድር ነው? የሆዴ ልጅ ሆይ፥ ምንድር ነው? የስእለቴ ልጅ ሆይ፥ ምንድር ነው? |
3 |
ጕልበትህን ለሴቶች አትስጥ፥ መንገድህንም ነገሥታትን ለሚያጠፉ። |
4 |
ለነገሥታት አይገባም፥ ልሙኤል ሆይ፥ ነገሥታት የወይን ጠጅ ይጠጡ ዘንድ አይገባም። መሳፍንትም። ብርቱ መጠጥ ወዴት ነው? ይሉ ዘንድ፤ |
5 |
እንዳይጠጡና ሕግን እንዳይረሱ፥ የድሀ ልጆችንም ፍርድ እንዳያጐድሉ። |
6 |
ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፤ |
7 |
ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጕስቍልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ። |
8 |
አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ። |
9 |
አፍህን ክፍት፥ በእውነትም ፍረድ፤ ለድሀና ለምስኪን ፍረድ። |
10 |
ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል። |
11 |
የባልዋ ልብ ይታመንባታል። ምርኮም አይጐድልበትም። |
12 |
ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም። |
13 |
የበግ ጠጕርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች። |
14 |
እርስዋ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፤ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች። |
15 |
ገና ሌሊት ሳለ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለገረዶችዋም ተግባራቸውን ትሰጣለች። |
16 |
እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፤ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች። |
17 |
ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥ ክንድዋንም ታበረታለች። |
18 |
ንግድዋ መልካም እንደ ሆነ ትመለከታለች፤ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም። |
19 |
እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ። |
20 |
እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች። |
21 |
ለቤትዋ ሰዎች ከበረዶ ብርድ የተነሣ አትፈራም፥ የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ የለበሱ ናቸውና። |
22 |
ለራስዋም ግብረ መርፌ ስጋጃ ትሠራለች ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች። |
23 |
ባልዋ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ይሆናል። |
24 |
የበፍታ ቀሚስ እየሠራች ትሸጣለች፥ ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች። |
25 |
ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፤ በኋላም ዘመን ላይ ትስቃለች። |
26 |
አፍዋን በጥበብ ትከፍታለች፤ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ። |
27 |
የቤትዋንም ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፥ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም። |
28 |
ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጋናዋንም ይናገራሉ፤ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል። |
29 |
መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። |
30 |
ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። |
31 |
ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፥ ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |