1 |
ከመኰንን ጋር ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥ በፊትህ ያለውን በደኅና አስተውል፤ |
2 |
ሰውነትህም ቢሳሳ፥ በጕሮሮህ ላይ ካራ አድርግ። |
3 |
ጣፋጩ መብል አይመርህ የሐሰት እንጀራ ነውና። |
4 |
ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። |
5 |
በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና። |
6 |
የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ |
7 |
በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። |
8 |
የበላኸውን መብል ትተፋዋለህ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋዋለህ። |
9 |
በሰነፍ ጆሮ አንዳች አትናገር፥ የቃልህን ጥበብ ያፌዝብሃልና። |
10 |
የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፤ ወደ ድሀ አደጎች እርሻ አትግባ፤ |
11 |
ታዳጊአቸው ጽኑ ነውና፥ እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና። |
12 |
ልብህን ለተግሣጽ ስጥ፥ ጆሮህንም ወደ እውቀት ቃል። |
13 |
ሕፃንን ከመቅጣት ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታው አይሞትምና። |
14 |
በበትር ትመታዋለህ፥ ነፍሱንም ትታደጋለህ። |
15 |
ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ቢሆን ልቤ ደግሞ ደስ ይለዋል፤ |
16 |
ከንፈሮችህም በቅን ቢናገሩ ኵላሊቶቼ ደስ ይላቸዋል። |
17 |
ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፤ |
18 |
በእውነት ፍጻሜ አለህና፥ ተስፋህም አይጠፋምና። |
19 |
ልጄ ሆይ፥ ስማ ጠቢብም ሁን ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ። |
20 |
የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ ለሥጋም ከሚሣሡ ጋር፤ |
21 |
ሰካርና ሆዳም ይደኸያሉና፥ የእንቅልፍም ብዛት የተቦጫጨቀ ጨርቅ ያስለብሳልና። |
22 |
የወለደህን አባትህን ስማ፥ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት። |
23 |
እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም። |
24 |
የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፥ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል። |
25 |
አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፥ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት። |
26 |
ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ፤ |
27 |
ጋለሞታ ሴት የጠለቀች ዐዘቅት ናትና፥ ሌላይቱም ሴት የጠበበች ጕድጓድ ናትና። |
28 |
እንደ ሌባ ታደባለች ወስላቶችንም በሰው ልጆች መካከል ታበዛለች። |
29 |
ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? |
30 |
የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን? |
31 |
ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ። |
32 |
በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል። |
33 |
ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል። |
34 |
በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥ በደቀልም ላይ እንደ ተኛ። |
35 |
መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፤ ጐሰሙኝ፥ አላወቅሁምም። መቼ እነሣለሁ? ደግሞ ጨምሬ እሻታለሁ ትላለህ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |