1 |
የለዘበች መልስ ቍጣን ትመልሳለች ሸካራ ቃል ግን ቍጣን ታስነሣለች። |
2 |
የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፤ የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል። |
3 |
የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ። |
4 |
ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል። |
5 |
ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው። |
6 |
በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኃጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው። |
7 |
የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፤ የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም። |
8 |
የኅጥኣን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። |
9 |
የኅጥኣን መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እርሱ ግን ጽድቅን የሚከተል ይወድዳል። |
10 |
ክፉ መቅሠፍት መንገድን በተወ ሰው ላይ ይመጣል፥ ዘለፋንም የሚጠላ ይሞታል። |
11 |
ሲኦልና ጥፋት በእግዚአብሔር ፊት የታወቁ ናቸው፤ ይልቁንም የሰዎች ልብ የታወቀ ነው። |
12 |
ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም፥ ወደ ጠቢባንም አይሄድም። |
13 |
ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፤ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች። |
14 |
የአዋቂ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፤ የሰነፎች አፍ ግን በስንፍና ይሰማራል። |
15 |
ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው። |
16 |
እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል። |
17 |
የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል። |
18 |
ቍጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል። |
19 |
የታካች መንገድ እንደ እሾህ አጥር ናት፤ የጻድቃን መንገድ ግን የተደላደለች ናት። |
20 |
ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል። |
21 |
ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፤ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል። |
22 |
ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል። |
23 |
ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፤ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው! |
24 |
በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል። |
25 |
እግዚአብሔር የትዕቢተኞች ቤት ይነቅላል፤ የባልቴትን ዳርቻ ግን ያጸናል። |
26 |
የበደለኛ አሳብ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናት፤ ያማረ ቃል ግን ጥሩ ነው። |
27 |
ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል፤ መማለጃን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል። |
28 |
የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል የኅጥኣን አፍ ግን ክፋትን ያፈልቃል። |
29 |
እግዚአብሔር ከኅጥኣን ይርቃል፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል። |
30 |
የዓይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥ መልካም ወሬም አጥንትን ያለመልማል። |
31 |
የሕይወትን ተግሣጽ የሚሰማ ጆሮ በጠቢባን መካከል ይኖራል። |
32 |
ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል። |
33 |
እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፤ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |