1 |
የሰሎሞን ምሳሌዎች። ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው። |
2 |
በኃጢአት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል። |
3 |
እግዚአብሔር የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፤ የኅጥኣንን ምኞት ግን ይገለብጣል። |
4 |
የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። |
5 |
በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል። |
6 |
በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤ የኅጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። |
7 |
የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኅጥኣን ስም ግን ይጠፋል። |
8 |
በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤ በከንፈሩ የሚሰንፍ ግን ይወድቃል። |
9 |
ያለ ነውር የሚሄድ ተማምኖ ይሄዳል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። |
10 |
በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፤ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል። |
11 |
የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ናት፤ የኃጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። |
12 |
ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች። |
13 |
በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፤ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው። |
14 |
ጠቢባን እውቀትን ይሸሽጋሉ፤ የሰነፍ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል። |
15 |
የባለጠጋ ሀብት ለእርሱ የጸናች ከተማ ናት፤ የድሆች ጥፋት ድህነታቸው ነው። |
16 |
የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፤ የኃጥእ ፍሬ ግን ለኃጢአት ነው። |
17 |
ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፤ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል። |
18 |
ጥልን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው፤ ሐሜትንም የሚገልጥ ሰነፍ ነው። |
19 |
በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው። |
20 |
የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፤ የኅጥኣን ልብ ግን ምናምን ነው። |
21 |
የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፤ ሰነፎች ግን ከልባቸው ጕድለት የተነሣ ይሞታሉ። |
22 |
የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም። |
23 |
ክፉ ነገር ማድረግ ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው፤ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው። |
24 |
የኀጥእ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፥ ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች። |
25 |
ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ኃጥእ አይገኝም፤ ጻድቅ ግን የዘላለም መሠረት ነው። |
26 |
ሆምጣጤ ጥርስን፥ ጢስም ዓይንን እንደሚጐዳ፥ እንዲሁም ታካች ለላኩት። |
27 |
እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፤ የኀጥኣን ዕድሜ ግን ታጥራለች። |
28 |
የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን ይጠፋል። |
29 |
የእግዚአብሔር መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፥ ጥፋት ግን ክፋትን ለሚያደርጉ። |
30 |
ጻድቃን ለዘላለም አይናወጡም፤ ኅጥኣን ግን በምድር ላይ አይቀመጡም። |
31 |
የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ ጠማማ ምላስ ግን ትቈረጣለች። |
32 |
የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፤ የኀጥኣን አፍ ግን ጠማማ ነው።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |