1 |
ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት። |
2 |
አሮንም። በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው። |
3 |
ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። |
4 |
ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው። |
5 |
አሮንም ባየው ጊዜ መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም።ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው ሲል አወጀ። |
6 |
በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ። |
7 |
እግዚአብሔርም ሙሴን። ከግብፅ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ ኃጢአት ሠርተዋልና ሂድ፥ ውረድ። |
8 |
ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፥ ሰገዱለትም፥ ሠዉለትም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ ሲል ተናገረው። |
9 |
እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። |
10 |
አሁንም ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። |
11 |
ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም። አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ? |
12 |
ግብፃውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። |
13 |
ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። |
14 |
እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ። |
15 |
ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። |
16 |
ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ። |
17 |
ኢያሱም እልል ሲሉ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን። የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ አለው። |
18 |
እርሱም። ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ አለው። |
19 |
እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥ ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው። |
20 |
የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣው። |
21 |
ሙሴም አሮንን። ይህን ታላቅ ኃጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ? አለው። |
22 |
አሮንም እንዲህ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ቍጣህ አይቃጠል፤ ይህ ሕዝብ ክፋትን እንዲወድድ አንተ ታውቃለህ። |
23 |
እነርሱም። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉኝ። |
24 |
እኔም። ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ከእርሱ ሰብሮ ያምጣልኝ አልኋቸው፤ ሰጡኝም፤ በእሳትም ላይ ጣልሁት፥ ይህም ጥጃ ወጣ። |
25 |
ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥ |
26 |
በሰፈሩ ደጅ ቆሞ። የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ! አለ፤ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። |
27 |
እርሱም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእናንተ ሰው ሁሉ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩም ውስጥ በዚህና በዚያ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፥ የእናንተም ሰው ሁሉ ወንድሙን ወዳጁንም ጎረቤቱንም ይግደል አላቸው። |
28 |
የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያም ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ። |
29 |
ሙሴም። ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ እያንዳንዳችሁ በልጃችሁና በወንድማችሁ ላይ ዛሬ እጃችሁን ለእግዚአብሔር ቅዱስ አድርጉ አለ። |
30 |
በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ። እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ አላቸው። |
31 |
ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ። ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ |
32 |
አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ። |
33 |
እግዚአብሔርም ሙሴን። የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። |
34 |
አሁንም ሂድ፥ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ አለው። |
35 |
አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |