1 |
ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል። |
2 |
በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፤ |
3 |
እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና። |
4 |
እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤ የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው። |
5 |
ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት። |
6 |
ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ |
7 |
እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። |
8 |
በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑት እንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ። |
9 |
የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ ሥራዬንም አዩ። |
10 |
ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር። ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ። |
11 |
ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |