1 |
ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እንዴት ቸር ነው። |
2 |
እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ። |
3 |
የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና። |
4 |
ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነውና። |
5 |
እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፥ ከሰው ጋርም አልተገረፉም። |
6 |
ስለዚህ ትዕቢት ያዛቸው፤ ኃጢአትንና በደልን ተጐናጸፉአት። |
7 |
ዓይናቸው ስብ ስለ ሆነ ወጣ፤ ልባቸውም ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ። |
8 |
አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ። |
9 |
አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ። |
10 |
ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤ |
11 |
እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ? ይላሉ። |
12 |
እነሆ፥ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ። |
13 |
እንዲህም አልሁ። በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። |
14 |
ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። |
15 |
እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር። |
16 |
አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ። |
17 |
ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ። |
18 |
በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። |
19 |
እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ። |
20 |
ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ። |
21 |
ልቤ ነድዶአልና፥ ኵላሊቴም ቀልጦአልና፤ |
22 |
እኔ የተናቅሁ ነኝ አላውቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ። |
23 |
እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። |
24 |
በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ። |
25 |
በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ? |
26 |
የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው። |
27 |
እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋኻቸው። |
28 |
ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |