1 |
አምላኬ ሆይ፥ ከጠላቶቼ አድነኝ፤ በላዬም ከቆሙት አስጥለኝ። |
2 |
ከግፍ አድራጊዎች ታደገኝ፥ ከደም ሰዎችም አድነኝ። |
3 |
እነሆ፥ ነፍሴን ሸምቀውባታልና፥ ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ። አቤቱ፥ በበደሌም አይደለም፥ በኃጢአቴም አይደለም። |
4 |
ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፥ ተቀበለኝ፥ እይም። |
5 |
አንተም አቤቱ፥ የኃያላን አምላክ፥ የእስራኤል አምላክ፥ አሕዛብን ሁሉ ትጐበኛቸው ዘንድ ተነሥ፤ ዓመፅ የሚያደርጉትን ሁሉ አትማራቸው። |
6 |
ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ። |
7 |
እነሆ፥ በአፋቸው አሰምተው ይናገራሉ፤ ሰይፍም በከንፈሮቻቸው አለ፤ ማን ይሰማል? ይላሉ። |
8 |
አንተ ግን አቤቱ፥ ትሥቅባቸዋለህ፥ አሕዛብንም ሁሉ ትንቃቸዋለህ። |
9 |
እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነውና ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ። |
10 |
የአምላኬ ቸርነቱ ይገናኘኛል አምላኬ በጠላቶቼ ላይ ያሳየኛል። |
11 |
ሕግህን እንዳይረሱ አትግደላቸው፤ አቤቱ ጋሻዬ፥ በኃይልህ በትናቸው አውርዳቸውም። |
12 |
ስለ አፋቸው ኃጢአት ስለ ከንፈራቸውም ቃል፥ መርገምንና ሐሰትን ስለሚናገሩ፥ በትዕቢታቸው ይጠመዱ። |
13 |
በቍጣ አጥፋቸው፥ እንዳይኖሩም አጥፋቸው፤ የያዕቆብም አምላክ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲገዛ ይወቁ። |
14 |
ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ። |
15 |
እነርሱም መብል ለመፈለግ ይበተኑ፤ ያልጠገቡ እንደ ሆነም ያንጐረጕራሉ። |
16 |
እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና። |
17 |
ረዳቴ ሆይ፥ ለአንተ ለአምላኬ እዘምራለሁ፤ አንተ፥ አምላኬ፥ መጠጊያዬ ምሕረቴም ነህና።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |