1 |
ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል። |
2 |
እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም። |
3 |
እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል። |
4 |
እኔስ። አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ። |
5 |
ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ። መቼም ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል? ይላሉ። |
6 |
እኔን ለማየት ቢገባ ከንቱን ይናገራል፤ ልቡ ኃጢአትን ሰበሰበለት፤ ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም። |
7 |
በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ይሾካሾኩብኛል፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ። |
8 |
ክፉ ነገር መጣበት፤ ተኝቶአል ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ። |
9 |
ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ። |
10 |
አንተ ግን አቤቱ፥ ማረኝ እመልስላቸውም ዘንድ አስነሣኝ። |
11 |
ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ አወቅሁ። |
12 |
እኔን ግን ስለ ቅንነቴ ተቀበልኸኝ፥ በፊትህም ለዘላለም አጸናኸኝ። |
13 |
ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአሔር ይባረክ። አሜን አሜን።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |