1 |
አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ። |
2 |
ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም አክብደህብኛልና። |
3 |
ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። |
4 |
ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና። |
5 |
ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ ሸተተ በሰበሰም፤ |
6 |
እጅግ ጐሰቈልሁ ተዋረድሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ። |
7 |
ነፍሴ ስድብን ተሞልታለችና፥ ለሥጋዬም ጤና የላትምና። |
8 |
ታመምሁ፤ እጅግም ተቸገርሁ፥ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽሁ። |
9 |
አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም። |
10 |
ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኃይሌም ተወችኝ፥ የዓይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ። |
11 |
ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ከቍስሌ ገለል ብለው ቆሙ፥ ዘመዶቼም ርቀው ቆሙ። |
12 |
ነፍሴንም የሚሹአት በረቱብኝ፥ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ፥ ሁልጊዜም በሽንገላ ይመክራሉ። |
13 |
እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ሆንሁ። |
14 |
እንደማይሰማ ሰው በአፉም ተግሣጽ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። |
15 |
አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፤ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ትሰማኛለህ። |
16 |
ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለሁና፥ እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። |
17 |
እኔስ ወደ ማንከስ ቀርቤአለሁና፥ ቍስሌም ሁልጊዜም በፊቴ ነውና። |
18 |
በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ። |
19 |
ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል፥ በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ። |
20 |
ጽድቅን ስለ ተከተልሁ፥ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል። |
21 |
አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፤ አምላኬ፥ ከኔ አትራቅ። |
22 |
አቤቱ መድኃኒቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |