1 |
እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። |
2 |
ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሎአልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ። |
3 |
የሞት ጣር ያዘኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፤ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ። |
4 |
የእግዚአብሔርንም ስም ጠራሁ። አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት። |
5 |
እግዚአብሔር መሓሪና ጻድቅ ነው፥ አምላካችንም ይቅር ባይ ነው። |
6 |
እግዚአብሔር ሕፃናትን ይጠብቃል፤ ተቸገርሁ እርሱም አዳነኝ። |
7 |
ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና፤ |
8 |
ነፍሴን ከሞት፥ ዓይኔንም ከእንባ፥ እግሬንም ከመሰናከል አድኖአልና። |
9 |
በሕያዋን አገር በእግዚአብሔር ፊት እሄዳለሁ። |
10 |
አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ፤ እኔም እጅግ ተቸገርሁ። |
11 |
እኔም ከድንጋጤዬ የተነሣ። ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው አልሁ። |
12 |
ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ? |
13 |
የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። |
14 |
በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ። |
15 |
የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው። |
16 |
አቤቱ፥ እኔ ባሪያህ ነኝ፥ ባሪያህ ነኝ፥ የሴት ባሪያህም ልጅ ነኝ፤ ሰንሰለቴን ሰበርህ። |
17 |
ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን እሠዋለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። |
18 |
በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ፥ |
19 |
በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፥ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በመካከልሽም። ሃሌሉያ
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |