1 |
ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |
2 |
ለእርሱም የኢዮሣፍጥ ልጆች ዓዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤል፥ ሰፋጥያስ የሚባሉ ወንድሞች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። |
3 |
አባታቸውም ብዙ ስጦታ፥ ብርና ወርቅ፥ የከበረም ዕቃ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሰጣቸው፤ መንግሥቱን ግን በኵር ልጁ ስለ ሆነ ለኢዮራም ሰጠ። |
4 |
ኢዮራምም በአባቱ መንግሥት ላይ ተነሥቶ በጸና ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉ ሌሎችንም የእስራኤልን መሳፍንት በሰይፍ ገደለ። |
5 |
ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። |
6 |
የአክአብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። |
7 |
ነገር ግን ከዳዊት ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን፥ ለእርሱና ለልጆቹም በዘመናት ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ስለ ሰጠው ተስፋ፥ እግዚአብሔር የዳዊትን ቤት ያጠፋ ዘንድ አልወደደም። |
8 |
በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዐመፀ፥ ለራሱም ንጉሥ አነገሠ። |
9 |
ኢዮራምም ከአለቆቹና ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ። |
10 |
ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፀ፥ በዚያንም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዐመፀ፥ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና። |
11 |
ዳግምም በይሁዳ ተራሮች ላይ መስገጃዎችን ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን እንዲያመነዝሩ አደረጋቸው፥ ይሁዳንም አሳተው። |
12 |
ከነቢዩም ከኤልያስ እንዲህ የሚል ጽሕፈት መጣባት። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥ |
13 |
በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥ የአክዓብም ቤት እንዳደረገ ይሁዳንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እንዲያመነዝሩ አድርገሃልና፥ ከአንተም የሚሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን ገድለሃልና፥ |
14 |
እነሆ፥ እግዚአብሔር ሕዝብህንና ልጆችህን ሚስቶችህንም ያለህንም ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይቀሥፋል። |
15 |
አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ በየዕለቱ እስኪወጣ ድረስ በክፉ የአንጀት ደዌ ትታመማለህ። |
16 |
እግዚአብሔርን የፍልስጥኤማውያንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረባውያንን መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሣ። |
17 |
ወደ ይሁዳም ወጡ፥ አፈረሱአትም፥ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ወንዶች ልጆቹንም ሴቶች ልጆቹንም ማረኩ፤ ከታናሹም ልጅ ከአካዝያስ በቀር ልጅ አልቀረለትም። |
18 |
ከዚህም ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር በማይፈወስ ደዌ አንጀቱን ቀሰፈው። |
19 |
ከቀንም ወደ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀቱ ወጣ፥ በክፉም ደዌ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርገው እንደ ነበር ለእርሱ የመቃብር ወግ አላደረገም። |
20 |
መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ሄደ፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |