1 |
የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ። |
2 |
ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን። ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ እግዚአብሔርን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ቍጣ ሆኖብሃል። |
3 |
ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድር አስወግደሃልና፥ እግዚአብሔርንም ትፈልግ ዘንድ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል አለው። |
4 |
ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ደግሞም ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር መለሳቸው። |
5 |
በምድር ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ። |
6 |
ፈራጆቹንም። ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ። |
7 |
አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉን ተጠንቅቃችሁ አድርጉ አላቸው። |
8 |
ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በእግዚአብሔር ስም ፍርድን እንዲፈርዱ ክርክርንም እንዲቈርጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። |
9 |
እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ እግዚአብሔርን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ። |
10 |
በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችሁ በደምና በደም መካከል በሕግና በትእዛዝ በሥርዓትና በፍርድም መካከል ያለ ማናቸውም ነገር ወደ እናንተ ቢመጣ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ፥ ቍጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። |
11 |
እነሆም፥ ለእግዚአብሔር በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |