1 |
የአካዝያስም እናት ጎቶልያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የመንግሥትን ዘር ሁሉ አጠፋች። |
2 |
የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ወስዳ ከተገደሉት ከንጉሥ ልጆች መካከል ሰረቀችው፤ እርሱንና ሞግዚቱንም ወደ እልፍኝ ወሰደች፥ እንዳይገደልም ከጎቶልያ ሸሸጉት። |
3 |
በእርስዋም ዘንድ ተሸሸጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች። |
4 |
በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ በካራውያንና በዘበኞች ላይ ያሉትን የመቶ አለቆች ወሰደ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት አገባቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አማላቸው፥ የንጉሡንም ልጅ አሳያቸው። |
5 |
እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲህ አድርጉ፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ የንጉሡን ቤት ዘብ ጠብቁ፤ |
6 |
ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ በሱር በር ሁኑ፤ አንዱም እጅ ከዘበኞች ቤት በኋላ ባለው በር ሁኑ፤ ቤቱንም ጠብቁ፥ ከልክሉም፤ |
7 |
ከእናንተም በሰንበት ቀን የምትወጡት ሁለቱ እጅ በንጉሥ ዙሪያ ሆናችሁ የእግዚአብሔርን ቤት ጠብቁ። |
8 |
ንጉሡንም በዙሪያው ክበቡት፥ የጦር ዕቃችሁም በእጃችሁ ይሁን፤ በሰልፋችሁ መካከል የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም በወጣና በገባ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁኑ። |
9 |
መቶ አለቆችም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ በሰንበት ይገቡ የነበሩትን፥ በሰንበቱም ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ። |
10 |
ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር ሁሉ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። |
11 |
ዘበኞቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር ዕቃቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ ቆሙ። |
12 |
የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፥ ምስክሩንም ሰጠው፤ ቀብተውም ንጉሥ አደረጉትና። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ እያሉ እጃቸውን አጨበጨቡ። |
13 |
ጎቶልያም የሠራዊቱንና የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች። |
14 |
እነሆም፥ ንጉሡ እንደ ተለመደው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ፥ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች፤ የአገሩም ሕዝብ ሁል ደስ ብሎአቸው ቀንደ መለከት ይነፉ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ። ዓመፅ ነው፥ ዓመፅ ነው ብላ ጮኸች። |
15 |
ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች። ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትንም በሰይፍ ግደሉት ብሎ አዘዛቸው፤ ካህኑ። በእግዚአብሔር ቤት አትገደል ብሎአልና። |
16 |
እጃቸውንም በእርስዋ ላይ ጫኑ፥ በፈረሱም መግቢያ መንገድ ወደ ንጉሥ ቤት ወሰዱአት፥ በዚያም ገደሉአት። |
17 |
ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን አደረገ፤ ደግሞም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን አደረገ። |
18 |
የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን አደቀቁ፥ የበኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ካህኑም ለእግዚአብሔር ቤት አስተዳዳሪዎችን ሾመ። |
19 |
መቶ አለቆቹንና ካራውያንንም፥ ዘበኞችንና የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረዱት፥ በዘበኞችም በር መንገድ ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ በነገሥታቱም ዙፋን ተቀመጠ። |
20 |
የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች። ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት አጠገብ በሰይፍ ገደሉአት።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |