1 |
በገለዓድ ቴስቢ የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን። በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም አለው። |
2 |
የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ለእርሱ መጣለት። |
3 |
ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፥ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ። |
4 |
ከወንዙም ትጠጣለህ፥ ቍራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ። |
5 |
ሄደም እንደ እግዚአብሔር ቃልም አደረገ። ሄዶም በዮርዳኖስ ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተቀመጠ። |
6 |
ቍራዎቹም በየጥዋትና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ከወንዙም ይጠጣ ነበር። |
7 |
ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረምና ወንዙ ደረቀ። |
8 |
ተነሥተህም በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፥ በዚያም ተቀመጥ፤ |
9 |
እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት ባልቴት አዝዣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣለት። |
10 |
ተነሥቶም ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልቴት በዚያ እንጨት ትለቅም ነበር፤ እርሱም ጠርቶ። የምጠጣው ጥቂት ውኃ በጽዋ ታመጭልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። |
11 |
ውኃም ልታመጣለት በሄደች ጊዜ ወደ እርስዋ ጠርቶ፥ ቁራሽ እንጀራ በእጅሽ ይዘሽ ትመጭ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። |
12 |
እርስዋም። አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ አለች። |
13 |
ኤልያስም አላት። አትፍሪ፤ ይልቅስ ሄደሽ እንዳልሺው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤ |
14 |
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም። |
15 |
እርስዋም ሄዳ እንደ ኤልያሳ ቃል አደረገች፤ እርስዋና እርሱ ቤትዋም ብዙ ቀን በሉ። |
16 |
በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም። |
17 |
ከዚያም በኋላ የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ትንፋሹም እስኪታጣ ድረስ ደዌው እጅግ ከባድ ነበረ። |
18 |
እርስዋም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው። |
19 |
ኤልያስም። ልጅሽን ስጪኝ አላት። ከብብትዋም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው በአልጋውም ላይ አጋደመው። |
20 |
ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ልጅዋን በመግደልህ ይህችን ትቀልበኝ የነበረቺቱን ባልቴት እንዲህ ደግሞ አስጨነቅኻትን? ብሎ ጮኸ። |
21 |
በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘረጋበት፥ ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጮኸ። |
22 |
እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እርሱም ዳነ። |
23 |
ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፥ ኤልያስም። እነሆ፥ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል ብሎ ለእናቱ ሰጣት። |
24 |
ሴቲቱም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን አወቅሁ አለችው።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |