1 |
የሳኦልም ልጅ ኢያቡስቴ አበኔር በኬብሮን እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ እጁ ደከመች፥ እስራኤላውያንም ሁሉ ደነገጡ። |
2 |
ለሳኦልም ልጅ ለኢያቡስቴ የጭፍራ አለቆች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ የአንዱም ስም በዓና፥ የሁለተኛውም ስም ሬካብ ነበረ፥ ከብንያምም ልጆች የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ነበሩ፤ ብኤሮትም ለብንያም ተቈጥራ ነበር። |
3 |
ብኤሮታውያንም ወደ ጌቴም ሸሽተው ነበር፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ተጠግተው ነበር። |
4 |
ለሳኦልም ልጅ ለዮናታን አንድ ሽባ የሆነ ልጅ ነበረው። የሳኦልና የዮናታን ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ፥ ሞግዚቱም አዝላው ሸሸች፤ ፈጥናም ስትሸሽ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜምፊቦስቴ ነበር። |
5 |
የብኤሮታዊውም የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ቀኑ ሲሞቅ ወደ ኢያቡስቴ ቤት መጡ፤ እርሱም በቀትር ጊዜ በምንጣፍ ላይ ተኝቶ ነበር። |
6 |
በረኛይቱም ስንዴ ታበጥር ነበር፥ አንቀላፍታም ተኝታ ነበር፤ ሬካብና ወንድሙ በዓናም በቀስታ ገቡ። |
7 |
ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ እርሱ በእልፍኙ በምንጣፉ ላይ ተኝቶ ሳለ መቱት፥ ገደሉትም፤ ራሱንም ቈርጠው ወሰዱት፥ በዓረባም መንገድ ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ። |
8 |
የኢያቡስቴንም ራስ ይዘው ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጡ፥ ንጉሡንም። ነፍስህን ይሻ የነበረው የጠላትህ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ እነሆ፤ እግዚአብሔርም ዛሬ ከሳኦልና ከዘሩ ለጌታችን ለንጉሥ ተበቀለለት አሉት። |
9 |
ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞት ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነ ሕያው እግዚአብሔርን! |
10 |
መልካም ወሬ የያዘ መስሎት። እነሆ፥ ሳኦል ሞተ ብሎ የነገረኝን የምስራቹ ዋጋ እንዲሆን ይዤ በጺቅላግ ገደልሁት። |
11 |
ይልቁንስ በቤቱ ውስጥ በምንጣፉ ላይ ንጹሑን ሰው የገደላችሁትን እናንተን ኃጢአተኞችንማ እንዴት ነዋ? ደሙን ከእጃችሁ አልሻውምን? ከምድርም አላጠፋችሁምን? |
12 |
ዳዊትም ጕልማሶቹን አዘዘ፥ ገደሉአቸውም፤ እጃቸውንና እግራቸውን ቈርጠው በኬብሮን በውኃ መቆሚያ አጠገብ አንጠለጠሉአቸው። የኢያቡስቴንም ራስ ወስደው በአበኔር መቃብር በኬብሮን ቀበሩት።
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |