1 |
ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች። |
2 |
የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም። |
3 |
ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት። |
4 |
ሴኬምም አባቱን ኤሞርን። ይህችን ብላቴና አጋባኝ ብሎ ነገረው። |
5 |
ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ። |
6 |
የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ። |
7 |
የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከምድረ በዳ መጡ፤ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ስንፍናን ስላደረገ አዘኑ፥ እጅግም ተቈጡ፤ እንዲህ አይደረግምና። |
8 |
ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ልቡ ተነድፎአልና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርስዋን ስጡት። |
9 |
ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ። |
10 |
ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም በፊታችሁ ናት፤ ኑሩባት፥ ነግዱም፥ ግዙአትም። |
11 |
ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ። በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ። |
12 |
ብዙ ማጫና እጅ መንሻ አምጣ በሉኝ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ፤ ይህችን ብላቴና ግን አጋቡኝ። |
13 |
የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤ |
14 |
እንዲህም አሉአቸው። እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና። |
15 |
እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤ |
16 |
ሴቶች ልጆቻችንን እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፤ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን። |
17 |
ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን። |
18 |
ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ። |
19 |
ብላቴናውም ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፤ እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ። |
20 |
ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ። |
21 |
እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፤ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፤ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ። |
22 |
ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፤ እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ። |
23 |
ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደ ሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ። |
24 |
ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ፤ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። |
25 |
ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤ |
26 |
ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። |
27 |
የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤ |
28 |
በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ። |
29 |
ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። |
30 |
ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ። በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ። |
31 |
እነርሱም። በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያደርግባትን? አሉ። a
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |