1 |
ይስሐቅ ሸምግሎ ዓይኖቹ ከማየት በፈዘዙ ጊዜ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ። ልጄ ሆይ አለው፤ እርሱም። እነሆ አለሁ አለው። |
2 |
እርሱም አለው። እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም። |
3 |
አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፤ |
4 |
ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ። |
5 |
ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም አደን አድኖ ሊያመጣ ወደ ምድረ በዳ ሄደ። |
6 |
ርብቃም ልጅዋን ያዕቆብን እንዲህ አለችው። እነሆ፥ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው። |
7 |
አደን አድነህ አምጣልኝ፥ ሳልሞትም በልቼ በእግዚአብሔር ፊት እንድባርክህ የጣፈጠ መብል አድርግልኝ ብሎ ሲነግረው ሰማሁ። |
8 |
አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እኔ በማዝዝህ ነገር ስማኝ፤ |
9 |
ወደ መንጋ ሄደህ ሁለት መልካካም ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እነርሱንም ጣፋጭ መብል ለአባትህ እንደሚወደው አደርጋለሁ፤ |
10 |
ለአባትህም፥ ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ታገባለታለህ። |
11 |
ያዕቆብም ርብቃን እናቱን አላት። እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጕራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፤ |
12 |
ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደሚዘብት እሆናለሁ፤ መርገምንም በላዬ አመጣለሁ፥ በረከትን አይደለም። |
13 |
እናቱም አለችው። ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፤ ቃሌን ብቻ ስማኝ፤ ሂድና አምጣልኝ። |
14 |
ሄዶም አመጣ፥ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም የጣፈጠውን መብል አባቱ እንደሚወደው አደረገች። |
15 |
ርብቃም ከእርስዋ ዘንድ በቤት የነበረችውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፥ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አለበሰችው፤ |
16 |
የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፤ |
17 |
የሠራችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራውን ለልጅዋ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው። |
18 |
ወደ አባቱም ገብቶ። አባቴ ሆይ አለው እርሱም። እነሆኝ፤ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አለ። |
19 |
ያዕቆብም አባቱን አለው። የበኵር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኽኝ አደረግሁ፤ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና በልና ተቀመጥ፥ ካደንሁትም ብላ። |
20 |
ይስሐቅም ልጁን። ልጄ ሆይ፥ እንዴት ፈጥነህ አገኘኸው? አለው። እርሱም። እግዚአብሔር አምላክህ ወደ እኔ ስለ አቀረበው ነው አለ። |
21 |
ይስሐቅም ያዕቆብን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ ወይም እንዳልሆንህ እዳስስህ ዘንድ ቅረበኝ አለው። |
22 |
ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም፥ እንዲህም። ይህ ድምፅ የያዕቆብም ድምፅ ነው፥ እጆች ግን የዔሳው እጆች ናቸው አለው። |
23 |
እርሱም አላወቀውም ነበር፤ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ነበሩና፤ ስለዚህም ባረከው። |
24 |
አለውም። አንተ ልጄ ዔሳው ነህን? እርሱም። እኔ ነኝ አለ። |
25 |
እርሱም። ከልጄ አደን እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አቅርብልኝ አለ። አቀረበለትም፥ በላም፤ የወይን ጠጅ አመጣለት፥ እርሱም ጠጣ። |
26 |
አባቱ ይስሐቅም። ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ ሳመኝም አለው። |
27 |
ወደ እርሱም ቀረበ፥ ሳመውም፤ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፥ ባረከውም፥ እንዲህም አለ። የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እርሻ ሽታ ነው፤ |
28 |
እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥህ፤ |
29 |
አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን። |
30 |
ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብም ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ከወጣ በኋላ፥ ወዲያው በዚያው ጊዜ ዔሳው ከአደኑ መጥቶ ገባ። |
31 |
እርሱም ደግሞ ጣፋጭ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አገባ፤ አባቱንም። አባቴ ይነሣ፥ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ከልጁ አደን ይብላ አለው። |
32 |
አባቱ ይስሐቅም። አንተ ማን ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ አለው። |
33 |
ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ እንዲህም አለ። ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣ ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ሆኖ ይኖራል። |
34 |
ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፥ አባቱንም። አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ አለው። |
35 |
እርሱም። ወንድምህ በተንኮል ገብቶ በረከትህን ወሰደብህ አለ። |
36 |
እርሱም አለ። በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፥ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፤ ብኵርናዬን ወሰደ፥ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ። ደግሞም። ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን? አለ። |
37 |
ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው። እነሆ፥ ጌታህ አደረግሁት፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥ በእህልም በወይንም አበረታሁት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግ? |
38 |
ዔሳውም አባቱን አለው። አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ። ዔሳውም ቃሉን አንሥቶ አለቀሰ። |
39 |
አባቱ ይስሐቅም መለሰ አለውም። እነሆ፥ መኖሪያህ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፤ |
40 |
በሰይፍህም ትኖራለህ፥ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለህ። |
41 |
ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፤ ዔሳውም በልቡ አለ። ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቦአል፥ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ። |
42 |
ለርብቃም ይህ የታላቁ ልጅዋ የዔሳው ቃል ደረሰላት፤ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አስጠርታ አስመጣችው፥ አለችውም። እነሆ፥ ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል። |
43 |
አሁንም ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ፤ ተነሣና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፤ |
44 |
በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ፥ የወንድምህ ቍጣ እስኪበርድ ድረስ፤ |
45 |
የወንድምህ ቍጣ ከአንተ እስኪመለስ ድረስ፥ ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፤ ከዚያም ልኬ አስመጣሃለሁ፤ በአንድ ቀን ሁለታችሁን ለምን አጣለሁ? |
46 |
ርብቃም ይስሐቅን አለችው። ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |