1 |
አብርሃምም ሸመገለ በዘመኑም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው። |
2 |
አብርሃምም ሎሌውን የቤቱን ሽማግሌ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው። |
3 |
እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ |
4 |
ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፥ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ። |
5 |
ሎሌውም። ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ አገር ከእኔ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ልጅህን ወደ ወጣህበት አገር ልመልሰውን? አለው። |
6 |
አብርሃምም አለው። ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፤ |
7 |
ከአባቴ ቤት ከተወለድሁባት ምድርም ያወጣኝ። ይህችንም ምድር እሰጥሃለሁ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፥ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ። |
8 |
ሴቲቱም ከአንተ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ከዚህ ካቀረብሁህ መሐላ ንጹሕ ነህ፤ ልጄን ግን ወደዚያ አትመልሰው። |
9 |
ሎሌውም ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች እጁን አደረገ ስለዚሁም ነገር ማለለት። |
10 |
ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል አሥር ግመሎችን ወስዶ፥ ከጌታውም ዕቃ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፤ ተነሥቶም ወደ መስጼጦምያ ወደ ናኮር ከተማ ሄደ። |
11 |
ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አስበረከከ። |
12 |
እንዲህም አለ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። |
13 |
እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ |
14 |
ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ። |
15 |
ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት። |
16 |
ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች። |
17 |
ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና። ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። |
18 |
እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው። |
19 |
እርሱንም ካጠጣች በኋላ። ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች። |
20 |
ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። |
21 |
ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። |
22 |
ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዮው ግማሽ ሰቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤ |
23 |
እንዲህም አላት። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፤ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን? |
24 |
አለችውም። እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ። |
25 |
በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን። |
26 |
ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ ። |
27 |
እንዲህም አለ። ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ። |
28 |
ብላቴናይቱም ሮጠች፥ ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገረች። |
29 |
ለርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ምንጭ ወደ ሰውዮው ሮጠ። |
30 |
ቀለበቱንና አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ፥ የእኅቱን የርብቃንም ነገር። ያ ሰው እንዲህ አለኝ ያለችውን በሰማ ጊዜ፥ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ፤ እነሆም፥ በውኃው ምንጭ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር። |
31 |
እርሱም አለው። አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ፥ ግባ፤ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኔም ቤቱን ለግመሎችህም ስፍራ አዘጋጅቼአለሁ። |
32 |
ሰውዮውም ወደ ቤት ገባ፥ ግመሎቹንም አራገፈ፤ ገለባና ገፈራም ለግመሎቹ አቀረበ፤ እግሩን ይታጠብ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ላሉት ሰዎች እግር ውኃ አቀረበ። |
33 |
መብልንም በፊቱ አቀረበለት፤ እርሱ ግን። ነገሬን እስክናገር ድረስ አልበላም አለ። እርሱም። ተናገር አለው። |
34 |
እርሱም አለ። እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ። |
35 |
እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው፥ አገነነውም፤ በጎችንና ላሞችን፥ ብርንም፥ ወርቅንም፥ ወንዶች ባሪያዎችንና ሴቶች ባሪያዎችን፥ ግመሎችንም አህዮችንም ሰጠው። |
36 |
ሣራም የጌታዬ ሚስት በእርጅናው ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፤ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው። |
37 |
ጌታዬም እንዲህ ሲል አማለኝ። እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ |
38 |
ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ፥ ለልጄም ሚስትን ውሰድለት። |
39 |
ጌታዬንም። ሴቲቱ ምናልባት ባትከተለኝሳ? አልሁት። |
40 |
እርሱም አለኝ። አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፥ መንገድህንም ያቀናል። ለልጄም ከወገኖቼ ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ፤ |
41 |
የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ነህ፤ ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ። |
42 |
ዛሬም ወደ ውኃው ምንጭ መጣሁ፥ እንዲህም አልሁ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፤ |
43 |
እነሆ፥ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፤ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ። ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ ስላት፥ |
44 |
እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ የምትለኝ፥ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ያዘጋጃት ሴት እርስዋ ትሁን። |
45 |
እኔም የልቤን መናገር ገና ሳልፈጽም፥ እነሆ፥ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች፥ ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች፤ እኔም። እስኪ አጠጪኝ አልኋት። |
46 |
ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ አወረደችና። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህንም ደግሞ አጠጣለሁ አለች፤ እኔም ጠጣሁ፥ ግመሎቼንም ደግሞ አጠጣች። |
47 |
እኔም። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም። ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ አለች፤ ቀለበትም አደረግሁላት፥ ለእጆችዋም አምባሮች አደረግሁላት። |
48 |
በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። |
49 |
አሁንም ቸርነትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፥ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ። |
50 |
ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ። ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎም ልንመልስልህ አንችልም። |
51 |
ርብቃ እንኋት በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን። |
52 |
የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። |
53 |
ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። |
54 |
እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም፥ ከዚያም አደሩ፤ ማልደውም ተነሡና። ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው ። |
55 |
ወንድምዋና እናትዋም። ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች አሉ። |
56 |
እርሱም። እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። |
57 |
እነርሱም። ብላቴናይቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ። |
58 |
ርብቃንም ጠርተው። ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋም። እሄዳለሁ አለች። |
59 |
እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። |
60 |
ርብቃንም መረቁአትና። አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት። |
61 |
ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። |
62 |
ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ፤ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። |
63 |
ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። |
64 |
ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች። |
65 |
ሎሌውንም። ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም። እርሱ ጌታዬ ነው አላት፤ እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። |
66 |
ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። |
67 |
ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፤ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። a
|
Amharic Bible (Selassie) 1962 |
Selassie 1962: © United Bible Societies 1962 |