A A A A A

መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዓመት ውስጥ

መስከረም 26

ኢሳይያስ 43:1-28
1. አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ።
2. በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም።
3. እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ።
4. በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ።
5. እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።
6. ሰሜንን። መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም። አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።
7.
8. ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ።
9. አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ ወገኖችም ይከማቹ፤ ከመካከላቸው፤ ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም እውነት ነው ይበሉ።
10. ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።
11. እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።
12. ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ።
13. ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው?
14. የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከለዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ።
15. ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
16. እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤
17. እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፤ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፤ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
18. የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ።
19. እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለህ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ።
20. ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፥ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል።
21.
22. ያዕቆብ ሆይ፥ አንተ ግን አልጠራኸኝም፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ደክመሃል።
23. ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቍርባን አላስቸገርሁህም በዕጣንም አላደከምሁህም።
24. ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርኸኝ፥ በበደልህም አደከምኸኝ።
25. መተላለፍህን። ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም አላስብም።
26. አሳስበኝ፥ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር።
27. ፊተኛው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፥ መምህሮችህም በድለውኛል።
28. ስለዚህ የመቅደሱን አለቆች አረከስሁ፥ ያዕቆብንም እርግማን፥ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ።

ኢሳይያስ 44:1-28
1. አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ።
2. የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ።
3. በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፥
4. በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ።
5. ይህ። እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፥ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም። እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል በእስራኤልም የቁልምጫ ስም ይጠራል።
6. የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።
7. እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ።
8. አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱ ጀምሬ አልነገርኋችሁምን? ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ የለም፤ ማንንም አላውቅም።
9. የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፥ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፤ ስለዚህ ያፍራሉ።
10. አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው?
11. እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፤ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ።
12. ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፥ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይራባል ይደክምማል፥ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል።
13. ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለካዋል፤ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል።
14. የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል።
15. ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፥ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል።
16. ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፥ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና። እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ ይላል።
17. የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል ወደ እርሱም እየጸለየ። አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል።
18. አያውቁም፥ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉ ልቦቻቸውን ጨፍነዋል።
19. በልቡም ማንም አያስብም። ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም።
20. አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም። በቀኝ እጄ ሐሰት አለ አይልም።
21. ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ ባሪያዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ያልተረሳ ትሆናለህ።
22. መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ።
23. ሰማያት ሆይ፥ እግዚአብሔር አድርጎታልና ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ።
24. ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?
25. የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፥ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፥ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤
26. የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፥ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን። የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፥ የይሁዳንም ከተሞች። ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ፤
27. ቀላዩንም። ደረቅ ሁን፥ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ እላለሁ፤
28. ቂሮስንም። እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን ። ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ።

መዝሙር 110:1-7
1. እግዚአብሔር ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።
2. እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ።
3. ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ።
4. እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም።
5. እግዚአብሔር በቀኝህ ነገሥታትን በቍጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል።
6. በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ ሬሳዎችንም ያበዛል፤ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል።
7. በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፤ ስለዚህ ራስ ከፍ ከፍ ይላል።

ምሳሌ 26:5-9
5. ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት።
6. በሰነፍ መልእክተኛ እጅ ነገርን የሚልክ እግሮቹን ይቈርጣል ግፍንም ይጠጣል።
7. እንደሚንጠለጠሉ የአንካሳ እግሮች፥ እንዲሁም ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።
8. ለሰነፍ ክብርን የሚሰጥ ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው።
9. እሾህ በስካር እጅ እንደሚሰካ፥ እንዲሁ ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።

ገላትያ 4:1-31
1. ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥
2. ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው።
3. እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤
4. ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤
5. እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ።
6. ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።
7. ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።
8. ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤
9. አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?
10. ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ።
11. ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ።
12. ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና። እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም።
13. በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥
14. በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ።
15. እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ።
16. እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?
17. በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ።
18. ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው።
19. ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል።
20. ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ።
21. እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ።
22. አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና።
23. ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል።
24. ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት።
25. ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና።
26. ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት።
27. አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል።
28. እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን።
29. ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው።
30. ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት።
31. ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።