መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዓመት ውስጥ


መስከረም 23


ማሕልየ መሓልይ 1:1-17
1. ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር።
2. በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና።
3. ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፤ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፤ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ።
4. ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፤ ንጉሡ ወደ ቤቱ አገባኝ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፤ በቅንነት ይወድዱሃል።
5. እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች።
6. ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና፤ ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፤ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፤ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም።
7. ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ ወዴት ታሰማራለህ? በቅትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ?
8. አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ።
9. ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ።
10. የጕንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው።
11. ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን።
12. ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ።
13. ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው።
14. ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው።
15. ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ዓይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው።
16. ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፤ አልጋችንም ለምለም ነው።
17. የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።

ማሕልየ መሓልይ 2:1-17
1. እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ።
2. በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት።
3. በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በልጆች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም በጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው።
4. ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው።
5. በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና።
6. ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች።
7. እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ።
8. እነሆ፥ የውዴ ቃል! በተራሮች ላይ ሲዘልል፥ በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል።
9. ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፤ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል።
10. ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
11. እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ።
12. አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ።
13. በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
14. በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ፥ ቃልሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ፥ ድምፅሽንም አሰሚኝ።
15. ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን።
16. ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፤ በሱፍ አበባዎች መካከልም መንጋውን ያሰማራል።
17. ውዴ ሆይ፥ ቀኑ እስኪነፍስ፥ ጥላውም እስኪሸሽ ድረስ ተመለስ፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋውን ወይም የዋላውን እምቦሳ ምሰል።

መዝሙር 104:1-9
1. ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ ክብርንና ግርማን ለበስህ።
2. ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፤ ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋህ፤
3. እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥
4. መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል።
5. ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት።
6. በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ።
7. ከዘለፋህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነግጣሉ፤
8. ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፤
9. እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ።

ምሳሌ 24:15-16
15. እንደ ኀጥእ በጻድቅ ቤት ላይ አትሸምቅ፤ ማደሪያውንም አታውክ።
16. ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል፤ ኀጥኣን ግን በክፉ ላይ ይወድቃሉ።

1 ቆሮንቶስ 11:17-34
17. ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚከፋ እንጂ ለሚሻል ስላልሆነ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ የማመሰግናችሁ አይደለም።
18. በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፥ በአንድ በኩልም አምናለሁ።
19. በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና።
20. እንግዲህ አብራችሁ ስትሰበሰቡ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም፤
21. በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል።
22. የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? አላመሰግናችሁም።
23. ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤
24. ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም። እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።
25. እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።
26. ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።
27. ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።
28. ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤
29. ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።
30. ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል።
31. ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤
32. ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን።
33. ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።
34. ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ።