መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዓመት ውስጥ


ታህሳስ 8


ዳንኤል 5:1-30
1. ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፥ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር።
2. ብልጣሶርም የወይን ጠጅ በቀመሰ ጊዜ ንጉሡና መኳንንቶቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ። አባቴ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ ያመጣቸውን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አምጡ ብሎ አዘዘ።
3. የዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጡትን የወርቁን ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቶቹም ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው።
4. የወይን ጠጅም እየጠጡ ከወርቅና ከብር ከናስና ከብረት ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ።
5. በዚያም ሰዓት የሰው እጅ ጣቶች ወጥተው በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ በመቅረዙ አንጻር ጻፉ፤ ንጉሡም የሚጽፉትን ጣቶች አየ።
6. የዚያን ጊዜም የንጉሡ ፊት ተለወጠበት፥ አሳቡም አስቸገረው፥ የወገቡም ጅማቶች ተፈቱ፥ ጕልበቶቹም ተብረከረኩ።
7. ንጉሡም አስማተኞቹንና ከለዳውያኑን ቃላተኞቹንም ያገቡ ዘንድ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ንጉሡም የባቢሎንን ጠቢባን። ይህን ጽሕፈት ያነበበ ፍቺውንም ያሳየኝ ሐምራዊ ግምጃ ይለብሳል፥ የወርቅም ማርዳ በአንገቱ ዙርያ ይሆንለታል፥ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል ብሎ ተናገረ።
8. የዚያን ጊዜም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ያነብቡ፥ ፍቺውንም ለንጉሡ ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም።
9. ንጉሡም ብልጣሶር እጅግ ደነገጠ፥ ፊቱም ተለወጠበት፥ መኳንንቶቹም ተደናገጡ።
10. ንግሥቲቱም ስለ ንጉሡና ስለ መኳንንቱ ቃል ወደ ግብዣ ቤት ገባች፤ ንግሥቲቱም ተናገረች እንዲህም አለች። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፤ አሳብህ አያስቸግርህ፥ ፊትህም አይለወጥ።
11. የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው በመንግሥትህ ውስጥ አለ፤ በአባትህም ዘመን እንደ አማልክት ጥበብ ያለ ጥበብና ማስተዋል እውቀትም ተገኘበት፤ አባትህ ንጉሡ ናቡከደነፆር የሕልም ተርጓሚዎችና የአስማተኞች የከለዳውያንና የቃላተኞች አለቃ አደረገው።
12. መልካም መንፈስ፥ እውቀትም፥ ማስተዋልም፥ ሕልምንም መተርጐም፥ እንቈቅልሽንም መግለጥ፥ የተቋጠረውንም መፍታት ንጉሡ ስሙን ብልጣሶር ብሎ በሰየመው በዳንኤል ዘንድ ተገኝቶአልና። አሁንም ዳንኤል ይጠራ፥ እርሱም ፍቺውን ያሳያል።
13. የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ንጉሡ ፊት ገባ፤ ንጉሡም ተናገረው ዳንኤልም እንዲህ አለው። ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ከማረካቸው ከይሁዳ ምርኮኞች የሆንህ ዳንኤል አንተ ነህን?
14. የአማልክት መንፈስ እንዳለብህ፥ እውቀትና ማስተዋልም መልካምም ጥበብ እንደ ተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ።
15. አሁንም ይህን ጽሕፈት ያነብቡ ዘንድ፥ ፍቺውንም ያስታውቁኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች ወደ እኔ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን የነገሩን ፍቺ ያሳዩ ዘንድ አልቻሉም።
16. አንተ ግን ፍቺን ትሰጥ ዘንድ፥ የተቋጠረንም ትፈታ ዘንድ እንድትችል ሰምቻለሁ፤ አሁንም ጽሕፈቱን ታነብብ ዘንድ፥ ፍቺውንም ታስታውቀኝ ዘንድ ብትችል፥ ሐምራዊ ግምጃ ትለብሳለህ፥ የወርቅም ማርዳ በአንገትህ ዙሪያ ይሆንልሃል፥ አንተም በመንግሥት ላይ ሦስተኛ ገዥ ትሆናለህ።
17. የዚያን ጊዜም ዳንኤል መለሰ በንጉሡም ፊት እንዲህ አለ። ስጦታህ ለአንተ ይሁን፥ በረከትህንም ለሌላ ስጥ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ ፍቺውንም አስታውቃለሁ።
18. ንጉሥ ሆይ፥ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር መንግሥትንና ታላቅነትን ክብርንና ግርማን ሰጠው።
19. ስለ ሰጠው ታላቅነት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ በፊቱ ይንቀጠቀጡና ይፈሩ ነበር፤ የፈቀደውን ይገድል፥ የፈቀደውንም በሕይወት ያኖር ነበር፤ የፈቀደውንም ያነሣ፥ የፈቀደውንም ያዋርድ ነበር።
20. ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው።
21. ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት እስኪያውቅ ድረስ ከሰው ልጆች ተይለቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፥ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
22. ብልጣሶር ሆይ፥ አንተ ልጁ ስትሆን ይህን ሁሉ እያወቅህ በሰማይ ጌታ ላይ ኰራህ እንጂ ልብህን አላዋረድህም።
23. የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፤ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም።
24. ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል፤ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል።
25. የተጻፈውም ጽሕፈት። ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል።
26. የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው።
27. ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው።
28. ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው።
29. የዚያን ጊዜም ብልጣሶር ለዳንኤል ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ማርዳም በአንገቱ ዙሪያ እንዲያደርጉለት አዘዘ፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ።
30. በዚያ ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ።

ዳንኤል 6:1-28
1. ዳርዮስም በመንግሥቱ ሁሉ ዘንድ እንዲሆኑ መቶ ሀያ መሳፍንት በመንግሥቱ ላይ ይሾም ዘንድ ወደደ።
2. መሳፍንቱም ሒሳቡን ያመጡላቸው ዘንድ፥ ንጉሡም እንዳይጐዳ ሦስት አለቆች በላያቸው አደረገ፤ ከእነርሱም አንደኛው ዳንኤል ነበረ።
3. ዳንኤልም መልካም መንፈስ ስላለው ከአለቆችና ከመሳፍንት በለጠ፤ ንጉሡም በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ይሾመው ዘንድ አሰበ።
4. የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበረና፥ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም።
5. እነዚያም ሰዎች። ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ።
6. የዚያን ጊዜም አለቆቹና መሳፍንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት። ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።
7. የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች። ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ።
8. አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ፥ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፥ ጽሕፈቱንም ጻፍ።
9. ንጉሡም ዳርዮስ ጽሕፈቱንና ትእዛዙን ጻፈ።
10. ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም።
11. እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት።
12. ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ። ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን? አሉት። ንጉሡም መልሶ። ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው አላቸው።
13. የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው። ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት።
14. ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፤ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ።
15. የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን። ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ አሉት።
16. የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም። ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ አለው።
17. ድንጋይም አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተደረገው እንዳይለወጥ በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው።
18. ንጉሡም ወደ ቤቱ ሄደ ሳይበላም አደረ፤ መብልም አላመጡለትም፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ።
19. በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ።
20. ወደ ጕድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም። የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው።
21. ዳንኤልም ንጉሡን። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።
22. በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው።
23. የዚያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፥ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፤ ዳንኤልም ከጕድጓድ ወጣ፥ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።
24. ንጉሡም አዘዘ፥ ዳንኤልንም የከሰሱ እነዚያን ሰዎች አመጡአቸው፥ እነርሱንና ልጆቻቸውንም ሚስቶቻቸውንም በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉአቸው፤ ወደ ጕድጓዱም መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶች ያዙአቸው አጥንታቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።
25. የዚያን ጊዜም ንጉሥ ዳርዮስ በምድር ሁሉ ላይ ወደሚኖሩ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ ወደሚናገሩ ሁሉ ጻፈ፥ እንዲህም አለ። ሰላም ይብዛላችሁ።
26. በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያው አምላክ ለዘላለም የሚኖር ነውና፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፥ ግዛቱም እስከ መጨረሻ ድረስ ይኖራል።
27. ያድናል ይታደግማል፥ በሰማይና በምድርም ተአምራትንና ድንቅን ይሠራል፥ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ አድኖታል።
28. ይህም ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ መንግሥት ኑሮው ተቃናለት።

መዝሙር 136:10-26
10. ከበኵራቸው ጋር ግብጽን የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
11. እስራኤልንም ከመካከላቸው ያወጣ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
12. በጸናች እጅ በተዘረጋችም ክንድ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
13. የኤርትራን ባሕር በየክፍሉ የከፈለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
14. እስራኤልን በመካከሉ ያሳለፈ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
15. ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
16. ሕዝቡን በምድረ በዳ የመራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
17. ታላላቅ ነገሥታትን የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
18. ብርቱዎችንም ነገሥታት የገደለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
19. የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
20. የባሳንን ንጉሥ ዐግን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
21. ምድራቸውን ርስት አድርጎ የሰጠ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
22. ለባሪያው ለእስራኤል ርስት፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።
23. እኛን በመዋረዳችን አስቦናልና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
24. ከጠላቶቻችንም እጅ አድኖናልና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
25. ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።
26. የሰማይን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።

ምሳሌ 29:12-13
12. መኰንን ሐሰተኛ ነገርን ቢያደምጥ፥ ከእርሱ በታች ያሉት ሁሉ ዓመፅኞች ይሆናሉ።
13. ድሀና ግፈኛ ተገናኙ፤ እግዚአብሔር የሁለቱንም ዓይን ያበራል።

2 ጴጥሮስ 2:1-22
1. ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤
2. ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል።
3. ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።
4. እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥
5. ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥
6. ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥
7. ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥
8.
9. ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤
10.
11. ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም።
12. እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤
13. የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤
14. ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው።
15. ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ፥
16. ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ።
17. ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው።
18. ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ።
19. ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው። አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና።
20. በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል።
21. አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።
22. ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።